ቀጥታ፡

በሰመራ ሎጊያ የከተሞች ፎረምን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል

ሰመራ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ በሰመራ ሎጊያ  የዘንድሮውን የከተሞች ፎረም በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን  የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዘንድሮን 10ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም አዘጋጅ በሆነው የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የቅድመ ዝግጅት የስራ ክንውን ሁኔታ ምልከታ ተካሂዷል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በወቅቱ አንደገለጹት፤ በሰመራ የዘንድሮውን የከተሞች ፎረም ለማስተናገድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ተመልክተዋል።

የፎረሙ ዐውደ ርዕይ ማሳያ ስፍራ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ከፎረሙ ጎን ለጎን በከተማው የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የቱሪዝም መስህቦች እንደሚጎበኙ አመላክተዋል ።

የዝግጅቱ ኮሚቴዎች አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊም በበኩላቸው 25 ሺህ ካሬ ላይ ያረፈው የዐውደ ርዕይ ቦታና የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

በፎረሙ 150 ከተሞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመው ሠመራ ሎጊያ ከተማ  የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ስራዎችን በማከናወን እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ፎረሙ  በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ባንድ ላይ ተገናኝቸው  ያላቸውን ልምድ የሚለዋወጡበት፣ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮች የሚቀርቡበት እንዲሁም የከተሞቻችን ውጤታማ ስራዎች በዐውደ ርዕይ በመቅረብ የሚታዩበትን ዕድል የሚፈጠርበት መሆኑን አብራርተዋል።

ከህዳር 6 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም  በሰመራ ሎጊያ ከተማ  አስተዳደር አስተናጋጅነት የተሰናዳው 10ኛው የከተሞች ፎረም  “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም