በኢትዮጵያ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና የታቀዱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገትና ብልፅግና ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና የታቀዱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገትና ብልፅግና ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ናቸው
ሀዋሳ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና የታቀዱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገትና ብልፅግና ትልቅ ተስፋ የሰነቁ መሆናቸው ተገለጸ።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት ሲሆን መንግስት በቀጣይም ሌሎች የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በዓለም ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ግዙፍ ኤርፖርት፣ የኒውክሌር ፕላንት፣ የጋዝ ፋብሪካ እና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚገነቡ ይሆናል።
በትላንትናው ዕለትም በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር የሚያመርተው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል።
በተመሳሳይ በአመት 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ፕሮጀክት ግንባታም አስጀምረዋል።
የእነዚህ የተመረቁትም ሆነ ግንባታቸው የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀከቶች እውን መሆን ከሀገር ልማትና ከዜጎች ተጠቃሚነት አንፃር ኢዜአ ከአዲስ አበባ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምሁራኑ በአስተያየታቸው በቅርቡ የተጠናቀቀውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ እንዲሁም ለግንባታ ዝግጁ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት መስፈንጠሪያ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ታፈሰ ማቲዮስ(ዶ/ር)፤ የግድቡ መጠናቀቅ በተበሰረበት ዕለት አዳዲስ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይፋ መደረጋቸው የኢትዮጵያን የመስራት አቅም ያስገነዘበና የማደግ ተስፋዋን ያመለካተ መሆኑን ገልጸዋል።
ለግንባታ የታቀዱ እና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የኢትዮጵያን እመርታዊ ለውጥና እድገት የሚያረጋግጡ እንደሚሆኑ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ምርጌሳ ካባ፤ በዕቅድ የተያዙና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በኢትዮጵያ የላቀ እድገትና ብልጽግና እንደሚኖር አይቀሬ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቶቹ መገንባት ከኢትዮጵያም ባለፈ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በራስ ሃብትና ጉልበት የመፈፀም አቅምና የማደግ ተስፋን የሚያመላክቱ ይሆናሉ ብለዋል።
ሌላኛው የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኤልያስ ጉዲሳ(ዶ/ር)፤ በመንግስት የተከናወኑ እና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ትልቅ ትርጉም እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት በመንግስት ጠንካራ አቋምና ቁርጠኝነት የህዝቡ ትብብር አስደናቂ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የሁላችንም ጥረትና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ልማትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተስፋዬ ሰመላ፤ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ በተለይም ለግብርናው እድገት ትንሳኤ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደምታወጣ አስታውሰው የፕሮጀክቱ ግንባታ እውን ሲሆን ይህንን ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታል ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ምህረተለአብ አብርሀም(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የእነዚህ ፕሮጀክቶች እውን መሆን የሚኖራቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በቀጣናው፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ጭምር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።