ቀጥታ፡

ሁለተኛው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤መስከረም 23/2018 (ኢዜአ)፦ሁለተኛው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት ከጥቅምት 3 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይደረጋል።

“አፍሪካውያንን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት የሚያፋጥኑበትን ክህሎቶች ማስታጠቅ” የሳምንቱ መሪ ሀሳብ ነው።

ሁነቱን ያዘጋጁት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው።

በሁነቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች እና የአባል ሀገራት ሚኒስትሮች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣ የልማት ተቋማት አመራሮች፣ መምህራን፣ ኢኖቬተሮች፣ የወጣት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ይሳተፉበታል።

የአህጉሪቷን የክህሎት ምህዳር በመቀየር የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣የስራ እድል ፈጠራን ማሳደግ እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ላይ የጋራ ትብብርን ማጠናከር የሁነቱ አበይት ትኩረት ነው።

የአፍሪካ ክህሎት ክፍተትን መሙላት፣የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ለክህሎት ልማት መጠቀም እና በአጀንዳ 2063 አማካኝነት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ላይ ውይይት ይደረጋል።

በሳምንቱ የሚኒስትሮች እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮች፣ የክህሎት አውደ ርዕዮች እና የገበያ ትስስር ሁነቶች እንዲሁም የወጣቶች እና የስራ ፈጣሪዎች ፎረም እንደሚካሄድ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፎረሙ የአፍሪካ ኢኖቬተሮች የስራ ውጤቶች የሚቀርቡበት መሆኑን ገልጿል።

የክህሎቶች ሳምንት ተሳታፊዎቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት እና በኢኖሼሽን ማዕከላት ውስጥ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው የሚገኙ የሰው ኃይል ልማት ስራዎች ይጎበኛሉ።

ሳምንቱ ሲጠናቀቅ የአፍሪካ ክህሎት ልማት አስመልክቶ የጋራ አቋም መገለጫ እና የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት ለአህጉሪቷ የኢንዱስትሪ እና ክህሎት አጀንዳ ተጨባጭ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑን ህብረቱ ገልጿል።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ክህሎቶች ሳምንት እ.አ.አ ኦክቶበር 2024 በጋና አክራ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም