ቀጥታ፡

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያ እና የቻይና ወዳጅነት የበለጠ እንዲያብብ ያደረገ ፕሮጀከት ነው - የቻይናው ጂሲኤል ኩባንያ ሊቀመንበር ዡ ጎንግሻን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ  የኢትዮጵያ እና ቻይና ወዳጅነት የበለጠ እንዲያብብ ያደረገ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የቻይናው ጂሲኤል ኩባንያ ሊቀመንበር ዡ ጎንግሻን ገለጹ።

ፋብሪካው በኢትዮጵያ እና ቻይና የኢነርጂ ትብብር አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍትም ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር በይፋ መርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይም አስቀምጠዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የሚገነባው የቻይናው ጂሲኤል ኩባንያ ሊቀመንበር ዡ ጎንግሻን ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ትብበር በጎዴ በረሃ ላይ የበለጠ አብቧል ሲሉ ገልጸዋል።


 

የፋብሪካው ግንባታ ፕሮጀክት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረና ታሪካዊ የሚባል እንደሆነ ጠቅሰው በሁለቱ ሀገራት ያላሰለሰ ጥራት ፕሮጀክቱ እውን መሆኑን አመልክተዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ የቤልት እና ሮድ ኢኒሼቲቭ የስኬት መገለጫና የአፍሪካና የቻይና የኢነርጂ ትብብር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ 55ኛ ዓመቱን ላስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትርጉም ያለው ስጦታ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ነዳጅ እና የጋዝ ፕሮጀክቶቹ በኢትዮጵያ መንግስት እና በጂሲኤል ኩባንያ ያለውን ጥልቅ መተማመንና ጠንካራ አጋርነት ያመላክታል ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል አመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆን መቻሏን ገልጸዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት በቤልት እና ሮድ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ከአፍሪካ ከሚገነቡ ግዙፍ የአፍሪካ የኢነርጂ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንና እ.አ.አ በ2027 ማብቂያ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።


 

ፕሮጀክቱ ከነዳጅ ፍለጋ እስከ ገበያ ማቅረብ የተሟላ የአቅርቦት እና ኢንዱስትሪ እሴት ሰንሰለት እንደሚፈጥርና ኢትዮጵያ በነዳጅና ጋዝ ያላትን የውጭ ጥገኝነት በመቀነስ የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽኗን ማሳካት እንደሚያስችላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኢነርጂ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ ብልጽግና እና የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር የያዘቸውን ራዕይ የሚያግዝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ጂሲኤል ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አደራ በውል ይገነዘባል ያሉት ሊቀ መንበሩ ፋብሪካውን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እና በፍጥነት ገንብቶ በማጠናቀቅ በትጋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ እና የቻይና የኢነርጂ ትብብር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ነው ያሉት።

ፋብሪካው የጂሲኤል ኩባንያ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ጅማሮ ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ ኩባንያው በተፈጥሮ ጋዝ ልማት፣ ኢነርጂ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት፣ ኬሚካል ምርቶች እና የተለያዩ ዘርፎች መስራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

ኩባንያው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢነርጂ አቅርቦት ለማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ እድገትን ለማሳለጥ እና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲቀየር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም