ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመሯጯ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት - አሊኮ ዳንጎቴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመሯጯ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት - አሊኮ ዳንጎቴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመሯጯ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን የዳንጎቴ ግሩፕ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ ገለጹ።
ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ተደራሽነት የማስፋት ፍላጎት እንዳለውም አመልክተዋል።
የዳንጎቴ ግሩፕ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሀገር ናት ብለዋል።
መንግስት ባደረጋቸው የሪፎርም ስራዎችና የኢኮኖሚው ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መሆን ለኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቁልፍ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጓ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትሮችን እንድትስብ ማድረጉን አመልክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ እና ለኢንቨስምንት ምቹ የሆኑ ሪፎርሞች ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዝግጁ የሆነች ሀገር እንድትሆን ትልቅ ድርሻ ማበርከቱን ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች የሚደነቁና የመንግስትን የመፈጸም አቅም አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በቅርቡ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መንግስት ለኢነርጂ ደህንነት መረጋገጥና የኢንዱስትሪ እድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ስራዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ መግቢያ በር እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።
የዳንጎቴ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትምንት ሆልዲንግ አጋርነት በአፍሪካ ኢንዱስትሪ እድገት እና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ የጋራ ራዕይ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን ነው ያብራሩት።
የዳንጎቴ ግሩፕ ያለውን ልምድ በመጠቀም የጋራ ሽርክና ስራው ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትራንፎርሜሽን እና የግብርና ምርማነት እድገት መሰረት እንዲሆን አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የማዳባሪያ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ አልፎም የጎረቤት ሀገራትን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንደሚያረጋግጥ ነው የገለጹት።
ዳንጎቴ ግሩፕ ዛሬ በሶማሌ ክልል ከሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ በተጨማሪ የተለያዩ የማዳባሪያ አይነቶች ማምረት የሚያስችለውን ኢንቨስትመንቶች የመጀመር ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው የኢትዮጵያን የማዳባሪያ ፍላጎት የሚያሟላና የምርት አቅምን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
የማዳበሪያ ፕሮጀክቱ ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ከሲሚንቶ በመጠቀል የተሰማራበት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው ኩባንያው በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የሲሚንቶ ምርት በእጥፍ የማሳደግ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።
ዳንጎቴ ግሩፕ የአፍሪካን ልማትና እድገት የሚያፋጥኑ ስራዎች ላይ መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰስ እንደሚቀጥልም አክለዋል።