ቀጥታ፡

ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር መስራት የኢትዮጵያውያን የሰርክ ስራ መሆን ይኖርበታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ማድረግና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር መስራት የዕለት ተዕለት ስራቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀው ወደ ስራ አስገብተዋል።

በተመሳሳይም በአመት 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ፕሮጀክትም አስጀምረዋል።

የዩሪያ ማዳበሪያ እና የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ የመሰረት ድንጋይም አስቀምጠዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አመርቂና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስራዎች ዛሬ መጀመራቸውን አመልክተዋል።

ስራዎቹን የስኬቶቻችን ማብሰሪያና የማንሰራራት መሻታችን አድርገን እንወስደዋለን ሲሉም ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያውያን ዛሬ ታላቅ ቀን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሮጀክቶቹ እውን መሆን ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ዛሬ በሶማሌ ክልል የታየው ብርሃን በመላ ኢትዮጵያ እስኪረጋገጥና እያንዳንዱን ዜጋ ካለበት የድህነት አረንቋ አውጥቶ ወደ ሚገባቸው የብልጽግናና የልማት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ በትጋት መስራትና የተጀመረውን ማጠናቀቅ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እኛ እንጀምራለን፣ እኛ ተግተን እንሰራለን እናም እኛ እንጨርሳለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስራዎቻችን ሁሉ ኢትዮጵያን ከፍ እናደርጋለን ብልጽግናን እናረጋግጣለን ብለዋል።


 

ኢትዮጵያውያን ለታላላቅ ስራዎች በመደመር የኢትዮጵያን ስም የማስጠራት፣ ከፍታዋን የማረጋገጥና ለልጆቻችን የተሻለች ኢትዮጵያን መስራት የሰርክ ስራቸው መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብልጽግና እና የጀመረችውን ስራ መጨረስ የማይቆም መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም አካል በቀና ልብ ለሀገር ልማትና እድገት በጋራ እንዲሰራ አሳስበዋል።

በሶማሌ ክልል የተበሰሩት ፕሮጀክቶች የብልጽግና ፓርቲ ሁሉን አቃፊነት በግልጽ የሚያመላክት መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያን ማንሰራራትና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም