ቀጥታ፡

በደብረማርቆስ ከተማ የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ ልማትና እድገትን የሚያፋጥኑ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - የከተማ አስተዳደሩ

ደብረ ማርቆስ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፡- በደብረማርቆስ  ከተማ የሰፈነውን ሰላም አስጠብቆ ልማትና እድገት በማፋጠን የሕዝቡን ተጠቃሚነት  ማረጋገጥ የሚያስችሉ  ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን  የከተማው አስተዳደር ገለጸ። 

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት  የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ዙር መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ያካሄደ ሲሆን፤ በቀረበው  የአስተዳደሩ የአሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት እቅድ ላይ  ውይይት አድርጓል።


 

በጉባዔው መድረክ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ እንደገለጹት፤ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ልማት በማካሄድ ሀገር ለማሻገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ያቀዳቸውን አሻጋሪና ዘላቂ የልማት እቅዶችን ከግብ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች የልማት ዘርፎች በክልል ደረጃ የታቀደውን የ25 ዓመት እቅድ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም አስጠብቆ በማፅናት የከተማውን ልማትና እድገት  በማፋጠን የሕዝቡን ተጠቃሚነት  ማረጋገጥ የሚያስችሉ   ተግባራት  እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።  

ይህንን  ለማሳካት በሚደረገው ጥረትም የምክር ቤት አባላት  የተጠናከረ የድጋፍ ክትትል ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባል ብዙአየሁ አያሌው፤ በአስተዳደሩ የቀረበው እቅድ የሚያሰራና የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ይህ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆንም  ድጋፍና ክትትል በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል ጌታቸው ህብስቱ ፤  እቅዱ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥን በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ድጋፋቸውን  እንደሚያጠናክሩ  ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም