ኢሬቻ አብሮነትንና ትብብርን በማጠናከር ለሀገር እድገት የላቀ አበርክቶ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ አብሮነትንና ትብብርን በማጠናከር ለሀገር እድገት የላቀ አበርክቶ አለው

አዲስ አበባ ፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፡- ኢሬቻ አብሮነትንና ትብብርን በማጠናከር ለሀገር እድገት የላቀ አበርክቶ እንዳለው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ሃላፊ ጀማል ጀምበሩ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ደረጃ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በተለያዩ ባህላዊ ትርኢቶች ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጀማል ጀምበሩ (ዶ/ር) የኦሮሞ ህዝብ ከገዳ ስርዓት በወረሰው የኢሬቻ በዓል በአንድነትና በአብሮነት ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ነው።
በዓሉ ለከተማዋ ትልቅ ፀጋን ይዞ የሚመጣ መሆኑን አንስተው በተለይም ቱሪስቶችን በመሳብ፣ የንግድ ተቋማትንና አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ለሀገራችን እድገት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው ብለዋል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመተባበር፤ የመረዳዳትና የአንድነትና የሰላም መድረክ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ታላቁ የህዳሴ ግድባችን በኢትዮጵያውያን ርብርብ በተጠናቀቀበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ደግሞ ልዩ ትርጉም ያሰጠዋል ብለዋል።
በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ አመራርና ነዋሪው ተቀናጅተው በመስራት በቂ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ እንግዶች ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የንግድ ተቋማት አቅማቸውን አጠናክረው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ነው ያሉት።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ሞጎሴ በበኩላቸው የኢሬቻ በዓል የመተባበር፣ የመረዳዳትና የአንድነት መድረክ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢሬቻ የሰላም፣ የእርቅ እና ሁሉንም ያለ ልዩነት የሚያሰባስብ በዓል ስለሆነ እሴቱን ጠብቀን ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ለኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ልምዳቸውን አጠናክረው የሞቀ መስተንግዶ በማድረግ የአብሮነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።