በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው - ቢሮው

ሾኔ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በማድረግ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻል መርሃ ግብር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር በወቅቱ እንደገለጹት መንግሥት የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፉን በማሻሻልና በማዘመን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
በክልሉ በተለይም ባለፉት አመታት ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፉን ለማሻሻልና ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዘርፉ ከተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ባለፈ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት መጎልበት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ የተገኘው አበረታች ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው የተቀናጀ ስራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ከዝርያ ማሻሻል ስራው በተጓዳኝ የእንስሳት ጤና ማስጠበቅና የመኖ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በበኩላቸዉ፡- በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ትግበራ ጋር በማስተሳሰር በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ የወተት፣ የንብና የማር መንደሮችን ማደራጀት መቻሉን ጠቅሰው ዘርፉ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች በማርባታቸው ከወተትና ከወተት ተዋጽኦ ንግድ የተሻለ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን የተናገሩት በሾኔ ከተማ ነዋሪ አቶ አሰፋ ደንበል ናቸው።
በዝርያ ማሻሻያ መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ላይ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ የግብርና መምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡