በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እያለሙ ያሉ ባለኃብቶች የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኙ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪም እየሆኑ ነው - ኮርፖሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እያለሙ ያሉ ባለኃብቶች የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኙ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪም እየሆኑ ነው - ኮርፖሬሽኑ
ሀዋሳ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እያለሙ ያሉ ባለኃብቶች የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኙ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆኑ እንደሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ጥራት ባለው አደረጃጀትና የአስተዳደር ሥርዓት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በማሟላት የISO 9001፡ 2015 የዕውቅና የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍፁም ከተማ፤ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እያለሙ ያሉ ባለኃብቶች የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት በማግኘት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ጥራት ባለው አደረጃጀትና የአስተዳደር ሥርዓት እውቅና ማግኘቱን አድንቀው የሀዋሳን ተሞክሮ ለሌሎችም ማስፋት ይገባል ብለዋል።
አሁን ላይ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በመግባት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አስኪያጅ ማቴዎስ አሸናፊ በበኩላቸው፤ የISO 9001: 2015 የዕውቅና የምስክር ወረቀት ለባለሀብቶች በሰዓትና በሌሎች መስፈርቶች የላቀ አገልግሎት መስጠትን የሚመለከት መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ክብረአብ አበራ፤ የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በቁርጠኝነት በመስራት የተለያዩ የISO የምስክር ወረቀቶች ባለቤት በመሆን ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የባለሀብቶች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ህብረት ለማ፤ የዕውቅና ምስክር ወረቀቱ አምራች ባለሀብቶች አሁን ላይ ባላቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ ይበልጥ ተፈላጊነታቸውን የሚጨምር ነው ብለዋል።