ኢሬቻ አብሮነት የሚገለጽበት ሀገራዊ እሴት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ አብሮነት የሚገለጽበት ሀገራዊ እሴት ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢሬቻ የህዝቦች አንድነትና አብሮነት የሚገለፅበት ሀገራዊ እሴት መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዓለምፀሐይ ሽፈራው ገለጹ።
የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ አርሰዲ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል፣ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።
የ2018 የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ደረጃ ተከብሯል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እንዳሉት የገዳ ስርዓት አንዱ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ የህዝቦች ትስስር የሚጠናከርበት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጸናበት ነው።
የምስጋና፣ የሠላም፣ የፍቅር እና የእርቅ በዓል የሆነው ኢሬቻ የአብሮነት መገለጫ የሆነ ሀገራዊ አሴት መሆኑን ተናግረዋል።
መዲናዋ በአዲስ ዓመት በርካታ በዓላትና ሁነቶችን በተሳካ መልኩ ማስተናገዷን ጠቁመው የኢሬቻን በዓል በዚሁ ልክ ማክበር አለብን ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተዋበችበትና ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ባጠናቀቅንበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ስሜትና ደስታን ይፈጥራል ነው ያሉት።
መዲናችን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቋንም ገልፀዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ እሸቱ ለማ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢሬቻ የፍቅር፣ የአንድነት እና የአብሮነት በዓል መሆኑን ጠቁመው በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ኢሬቻ ሁሉም ህብረተሰብ የሚሳተፍበት እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በአከባበሩ ላይ ከተገኙት መካከል ወይዘሮ ፋይዛ ሙስጠፋ ኢሬቻ ሁላችንም ያለምንም ልዩነት የምናከብረው በዓል ነው ብለዋል።
አቶ ሽመልስ ተስንቱ በበኩላቸው የሁላችንም መገለጫ የሆነውን ኢሬቻን ከነትውፊቱ ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ነው ያሉት።
አቶ ፀሐይ መርጋ በበኩላቸው ኢሬቻ መተሳሰብና መቀራረብ እንዲሁም አብሮነት የሚጎላበት መሆኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ አየለች በየነም እንዲሁ ኢሬቻ ኢትዮጵያን በባህል ቱሪዝም ለዓለም የሚያስተዋውቅ መሆኑን ተናግረዋል።