በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ጸጋዎችን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ጸጋዎችን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ጸጋዎችን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ጸጋዎችን በማልማት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የአመራሩን አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ክልሉ ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ለመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ያዘጋጀው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተሰጠ ነው።
አቶ ገብረመስቀል ጫላ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ያሉትን ዕምቅ ጸጋዎች በማልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
ለዚህም በተለይ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ጸጋዎችን አልምቶ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉ መንግስት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለስኬታማነቱ የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የአመራሩን ብቃት የሚያሳድጉ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመው፣ ዛሬ የተጀመረው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት አመራሩ የነበረውን ትጋት እንዲያጠናክር ስልጠናው ያግዛል ብለዋል።
በተጨማሪም ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ፣ ፀጋዎችንና ዕድሎችን ለይቶ ለልማት የሚያውል እንዲሁም ፈተናዎችን ወደ ዕድል የሚቀይር አመራር በመፍጠር ውጤታማነትን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል።
በክልሉ የታቀዱ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በተቀናጀ መንገድ መመራት እንዳለባቸው አንስተው፣ ለዚህም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለሥራ ሃላፊዎች ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው የማደግና የለውጥ ሂደትን በተፈለገው ፍጥነትና መጠን ለማስኬድ አስተሳሰብን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለውጤት የእይታ ለውጥ ማድረግ ቀዳሚ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፣ የአዕምሮ እይታ ሲያድግ በተሰማራንበት ሁሉ ከፍ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ የእንችላለን ስሜት ይዳብራል ብለዋል።
ይህም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ልዕልና ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።
ያደጉ ሀገራት ሁሉ ለራሳቸው የነበራቸውን ዝቅተኛ አመለካከት በእንችላለን በመቀየራቸው ማደጋቸውን አስታውሰው የሁሉም ሰው የእይታ ለውጥ ለግልም ሆነ ለሀገራዊ ዕድገት አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል።
ሰልጣኝ አመራሮችም ዕይታቸውን በማሳደግና ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አሻግሮ በማየት የለውጥ ጉዞን ለማፋጠን መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት እየተሰጠ ባለው ስልጠና የማዕከላትና የዞን እንዲሁም የሦስቱ ሪጂዮ ፖሊስ ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።