ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘው ዕውቅና ኢትዮጵያ በመድሃኒት ቁጥጥር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ያሳያል - ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘው ዕውቅና ኢትዮጵያ በመድሃኒት ቁጥጥር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ያሳያል - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅት ያገኘችው ዕውቅና በመድሃኒት ቁጥጥር ዘርፍ ሊደረስበት ለታሰበው ስኬት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆናችንን የሚያሳይ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
እንደ ሀገር ተኪ ምርትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት የበለጠ የሚያግዝና የሀገር ወስጥ የመድሃኒት አምራቾችን የሚያበረታታ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በመድሃኒትና በህክምና መሳሪያ ቁጥጥር የደረሰችበት ስኬት ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርዓት ለመፍጠር ተግባራዊ የሆኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሯ ይህንን ደረጃ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ ከውጭ የሚገቡ መድሀኒቶችና ክትባቶች ዓለም አቀፍ ጥራትን፣ ብቃትንና ደህንነትን ያሟሉ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መሰራቱ ለውጤቱ መገኘት ምክንያት ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለኢትዮጵያ የሦስተኛ ደረጃን ሲሰጥ በመድሃኒት የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን አሰራር በአግባቡ ፈትሾ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በህክምና መሳሪያ ቁጥጥር የዓለም ጤና ድርጅትን የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለሀገራት የደረጃ ሦስት ዕውቅና የሚሰጠው የተረጋጋ፣ የተቀናጀና በአግባቡ የሚመራ የቁጥጥር ስርዓት መኖሩን ሲያረጋግጥ ነው።