ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው - የዓለም ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው - የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርትና ማህበራዊ ጥበቃ ሰብዓዊ ልማት መርሃ ግብር እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኤርትራ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኤርትራ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም በዚህ ወቅት፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ መንፈስ፣ አንድነትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን ታሪካዊ የድል አሻራ ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ ልማት ማሻሻያ መርሃ ግብሮች የሀገራትን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በጤና እና ማህበራዊ ጥበቃ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ላይ እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገቧን ተናግረዋል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ልማት ለማሻሻል ለትምህርትና ጤና ተደራሽነት፣ ለማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ በሰጠው ድጋፍ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመድኃኒት ቁጥጥር ሥርዓት ደረጃ-3 ውስጥ መካተቷ አስተማማኝና ጠንካራ የጤና ስርዓትን በመዘርጋት
ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ የህክምና አምራቾችን በማነቃቃት ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት በትምህርትና በጤና ተደራሽነት የእናቶችና ህፃነትን ሞት በመቀነስ ያስመዘገበችውን ውጤት ለማስቀጠል የዓለም ባንክ ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የዓለም ባንክ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ፤ ሰብዓዊ ልማትን ለማሳደግ በጤና፣ ትምህርትና ማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ አካታችነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ለእናቶችና ህጻናት የሚደረገው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ስኬት ድጋፍ ያደረጉ አጋር አካላት ምስጋና ይገባቸዋል፤ ድጋፉም ተጠናከሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ፎረሙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎችን በማሳተፍ የኢትዮጵያን የሰው ሀብት ልማት ማሻሻል የሚያስችሉ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ላይ መወያየት የሚያስችል ነው፡፡