ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ነው - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 የመንግሥት ከፍተኛ አመራር አባላትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።


 

"ክህሎቶችን መገንባት፣ ሥራዎችን ማቀላጠፍ፣ ልማትን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ፎረም ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ይቆያል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ውጤቶች ተገኝተዋል።

አጠቃላይ የብልጽግና እድገት እይታው ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ማድረግ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት፣ የማህበራዊ ልማትን በተለይም የሰብዓዊ ልማትን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለማህበራዊ ጥበቃ ዋስትና እና ለስራ እድል ፈጠራ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

በከተማና በገጠር ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በተለይም በትምህርት ልማት፣ በጤና ዘርፍ፣ የማህበራዊ ዋስትና ጥበቃን በማረጋገጥ በኩል በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም የዜጎችን ክህሎት በማሳደግ ብቁ አምራች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሀገራት የሰብዓዊ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን ካከናወኑ ለኢኮኖሚ እድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያመለክታል ሲሉም ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ልማት ደረጃ በአደጉና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ልዩነት የሚፈጥር ዋና ጉዳይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በመከናወን ላይ ለሚገኙ ስራዎች የዓለም ባንክ በሁሉም ዘርፎች መዋዕለ ንዋይና የቴክኒክ ድጋፍ በማቅረብ ትልቁ አጋር መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ መካሄዱ ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁለንተናዊ ብልጽግና የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ ልምድ እንደሚገኝበትም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም