ቀጥታ፡

የእንስሳትን ምርት፣ ጥራትና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ሂደትን የማዘመን ተግባር እየተከናወነ ነው - ባለስልጣኑ

ቢሾፍቱ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ የእንስሳትን ምርት፣ ጥራትና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ከምርት እስከ ማጓጓዝ ያለውን ሂደት ማዘመን ላይ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለፀ። 

ባለስልጣኑ በኢንዱስትሪ ደረጃ እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖን ከሚያመርቱ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በምርት ጥራትና ደህንነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ዛሬ አካሄዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለስልጣኑ የግብርና ምርቶች ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ የቁጥጥር ስራን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ጥራቱን ለማረጋገጥም ከጥሬ ምርቱ እስከ እሴት ሰንሰለቱ ያለው ሂደት ላይ የቁጥጥር ስራ መስራቱን አንስተዋል።


 

በኢንዱስትሪ ደረጃ እንስሳትን የሚያደልቡ፣ ወተት፣ ዶሮና የዶሮ ውጤቶች በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አካላት የምርቶቻቸውን ጥራትና ደህንነት በማረጋገጥ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መሰራቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የቁም እንስሳትን ጨምሮ ስጋና የስጋ ተረፈ ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ በማምረት ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

አምራቾቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በምርት ጥራትና ደህንነት ላይ በትብብር በመስራት ከማምረት እስከ ማጓጓዝ  ያለውን ሂደት ማዘመን ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ የምርት ማከማቻዎች መገንባትና ምርቱ ከባዕድ ነገር እንዳይቀላቀል መጠበቅ እንዲሁም ጤንነቱን  ማረጋገጥ ላይ መስራት አስገዳጅ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በእንስሳት መኖ ጥራትና ጤንነት ላይ በትኩረት መስራት ሌላኛው መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የኢትዮ ቺክን የላቦራቶሪ ቁጥጥር ማኔጀር ዶክተር ማህደር ታደሰ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ደረጃውን የጠበቀ፣ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ምርት ለተጠቃሚ ህብረተሰብ ለማድረስ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፣ ከኢትዮጵያ እንስሳት ጤና ኢንስቲትዩትና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራታቸውን አንስተዋል።

የአልማ ፋርም ዳይሬክተር ኢዮብ ኢቲቻ እንደገለፁት ጥራቱን የጠበቀ ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በምርት ጥራት ላይ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም