በደብረ ብርሃን ከተማ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጠ
ደብረ ብርሃን፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሃን ከተማ ባለፉት ሦስት ወራት 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ ተገለጸ።
ወደ ግንባታ የገቡ ባለሀብቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል የፕሮጀክቶችን ግንባታ ፈጥነው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ ተወካይ ውነቱ አሰፋ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የደብረ ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነች መጥታለች።
በዚህም ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 24 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ይነሳ የነበረው የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ታግዞ መፍታት መቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፈቃድ የተሰጣቸው ፈጥነው ወደ ግንባታ እንዲገቡ፣ በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩም እንዲያመርቱና ወደ ምርት የገቡትም በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ሚና እንደነበረው አስረድተዋል።
ፈቃድ ለተሰጣቸው ባለሃብቶችም የቦታ፣ የገንዘብ ብድርና ሌሎች ጥያቄዎችን ፈጥኖ በመፍታት ወደ ግንባታ ሥራ እንዲሸጋገሩ ተገቢ ድጋፍና ክትትል መደረጉን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ 161 ተቋማት ግንባታቸውን አጠናቀው ማሽን በመትከል ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ፈቃድ ወስደው ወደ ልማት ከገቡ ባለሀብቶች መካከል የብራውን ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ አብርሃም እንደገለጹት፣ በተደረገልን ድጋፍና ክትትል የፋብሪካውን ግንባታ ፈጥነን በማጠናቀቅ ለማምረት እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።
ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባም በዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ ከአርሶ አደሩ በመረከብ በቫይታሚን የበለፀገ የዳቦና የገንፎ ዲቄት እንዲሁም ብቅል በጥራትና በስፋት ያመርታል ብለዋል።
በተጨማሪም ለሕፃናት አልሚ ምግብ በማምረት በስርአተ ምግብ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ጠቁመዋል።
የደዴ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋበሪካ ሥራ አስኪያጅ ዮርዳኖስ ሙሉጌታ በበኩላቸው ፋብሪካው የተለያየ ይዘትና መጠን ያላቸውን ጠርሙስና ብርጭቆዎች በማምረት ከውጭ የሚገባን ምርት ለመተካት ያለመ ነው።
በአሁኑ ወቅት የፋብሪው ግንባታ ተጠናቆ ማሽኖችን በመትከል ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ፋብሪካው በቀጣይ 2 ወራት ውስጥ ወደ ማምረት ሥራ እንደሚሸጋገር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፈጠረው መነቃቃት በተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦትና ሌሎች ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ ማድረጉን አስረድተዋል።
በደዴ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ በኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ሥራ ዘርፍ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ዮናስ ሸዋንግዛው በበኩሉ ሰርቶ ከሚያገኘው ገቢ ባለፈ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ማግኘቱን ተናግሯል።
በደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ከ600 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።