ሰላምን ለማፅናት ድጋፍና ክትትላችንን አጠናክረናል- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለማፅናት ድጋፍና ክትትላችንን አጠናክረናል- የምክር ቤት አባላት

ሰቆጣ ፤ መስከረም 22/2018 (ኢዜአ) ፡- የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት የአካባቢያው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ድጋፍና ክትትላቸውን ይበልጥ ማጠናከራቸውን ገለጹ።
በአማራ ክልል በየደረጃው ሕዝባዊ ውይይቶች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላምን ለማፅናት ያለውን ቁርጠኝነት በይፋ አሳይቷል።
ይህንን ቁርጠኝነት ካሳዩ የክልሉ አከባቢዎች መካከል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ይገኝበታል።
በአስተዳደሩ ምክር ቤት የደሃና ወረዳ ተወካይ አቶ ፋንታው የኋላው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በነበረው ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ይህንን ለመከላከል ሕዝባዊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በዚሀም ሕብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ሰላምን አፅንቶ እንዲቀጥል ድጋፍና ክትትላቸውን በማጠናከር ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማሕበረሰቡ በመቀላቀል ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው በምክር ቤቱ የአበርገሌ ወረዳ ተወካይ አቶ ሸጋው ተበጀ በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ ሰፍኖ ያለውን ሰላምን አፅንቶ ለማስቀጠል ድጋፍና ክትትላቸውን ማጠናከራቸውን ገልጸዋል።
የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበትም ከአጎራባች ዞኖች ጋር ተቀናጅተን ለመስራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢያቸው ሰላም ፀንቶ በመቀጠሉ ለልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የተናገሩት የጋዝጊብላ ወረዳ ተወካይ ወይዘሮ አጫዋች ዘገየ ናቸው።
የተገኘውን ለውጥ በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ ስራዎች እንዲከናወኑ በመደገፍ እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታይቱ ካሴ፤በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችና አባላት የሰላም ግንባታ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሰላምን የማፅናቱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።