የኢሬቻ እሴቶች ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያላት ሀገር ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ እሴቶች ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያላት ሀገር ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢሬቻ ባህላዊ እሴቶች ጠንካራ ወንድማማችነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያላት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያግዙ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ኢሬቻ የምስጋና በዓል፣ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።
የ2018 የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደረጃ ተከብሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ማሾ ኦላና በዚሁ ወቅት፤ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው ኢሬቻ የህዝቦች ትስስር የሚጠናከርበት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጸናበት በዓል ነው ብለዋል።
ኢሬቻ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚያከብሩትና በርካታ የዓለም ቱሪስቶች የሚታደሙበት መሆኑን በማንሳት፥ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የኢትዮጵያ ድንቅ ባህል ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ ለመዲናዋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለቱሪዝም ፍሰት መጨመር ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የዕርቅ ሀገራዊ እሴቶች ጎልተው የሚንጸባረቁበት መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ የኢሬቻ እሴቶች የበለጸገችና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያላት ሀገር ለመገንባት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዘሪሁን ኮርሜ፥ ኢሬቻ የአብሮነት፣ የምስጋና እና የመልካም ምኞት መግለጫ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በሆረ ፊንፊኔ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የእንግዳ ተቀባይነት እሴቱን ማጎልበትና አብሮነትን ማጉላት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የበዓሉ ታዳሚ ውዱ አሰፋ እንዳሉት ኢሬቻ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በአብሮነትና በወንድማማችነት የሚከብሩት በዓል ነው፡፡
መሐመድ አብዱልቃድር በበኩላቸው ኢሬቻ በህብረት የሚከበር የፍቅር፣ የሰላምና ኢትዮጵያ ካሏት አስደናቂ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ኢሬቻ የፍቅር መገለጫ እንዲሁም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚያሰባስብ በዓል መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ እጸገነት በሪሁን ናቸው፡፡
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ እሑድ መስከረም 25 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።