አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመዲናዋ የስማርት ሲቲ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመዲናዋ የስማርት ሲቲ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለመዲናዋ የስማርት ሲቲ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ ገለጹ፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን፣ ተአማኒ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት ሚያዚያ 2017 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ዜጎች በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሚገጥማቸውን እንግልትና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ሁሉም አካካቢ ለመፍታት አዲስ አበባን ጨምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የራሳቸውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እያስጀመሩ ነው፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዜጎች የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሥራ አስጀምሯል።
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሥነ ምግባር የታነጹና ለሙያው በቂ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ 13 የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት በዲጂታል የታገዘ የተቀናጀ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡
የተወሰኑ የፌደራል ተቋማትም በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ ለዜጎች የተሟላ የመንግስት አገልግሎት በመስጠት የመዲናዋን ስማርት ሲቲ ግንባታ የሚያግዝና የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኢኮኖሚ፣ ቤቶችና ትራንስፖርት እንዲሁም መሬትና ግንባታ ዘርፎች ተከፋፍሎ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንዲዋቀር የሚያስችል አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሶብ አገልግሎት በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡
በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 107 የከተማ አስተዳደሩና የፌደራል ተቋማት አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወቃል።