ለሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
ለሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ ተገብቷል
አዲስ አበባ፣መስከረም 22/2018 ዓ.ም (ኢዜአ):-በቀጣይ ለሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ መገባቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፥ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓላት አከባበርን በተመለከተ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በዋና መሥሪያ ቤቱ ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ወቅት በሰጡት የሥራ መመሪያ የፀጥታና ደህንነት መዋቅሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ኃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ በመሆኑ አጠቃላይ ያለፉት ሁነቶች በመላው ሀገሪቱ በሰላም መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓላትም በሰላም እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም የበዓላቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የፀጥታ ኃይሉ ከሕብረተሰቡ ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢሬቻ ባህልና እሴት ከሚፈቅደው ውጪ በማንኛውም ሁኔታ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን፣ ስለታማ፣ተተኳሽና ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የበዓሉ ታዳሚዎችም ለፀጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።