የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የሰው ሃብት ልማትን ማጠናከር ወሳኝ ነው- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የሰው ሃብት ልማትን ማጠናከር ወሳኝ ነው- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የሰው ሃብት ልማትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
"ክህሎቶትን መገንባት፣ ሥራዎችን ማቀላጠፍ፣ ልማትን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሰው ሃብት ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥርዓተ ምግብና በማህበራዊ ጥበቃ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም በሌማት ትሩፋት፣ ኢትዮጵያ ታምርት፣ አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ሀገራዊ የልማት መርሃ ግብሮች የተመዘገቡ ስኬቶች የሰው ሀብት ልማትን በማጠናከርና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ውጤቶችን አስገኝተዋል ብለዋል።
ለሰው ሀብት ልማት በተሰጠው ትኩረት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የሰው ሀብት ልማት ለማጠናከር ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ የሰው ሀብት ልማት ድህነትን በማሸነፍ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሁነኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበራዊ ዘርፎች የሰው ሃብት ልማትን የሚያጎለብቱ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ግንባታ የጀመረቻቸውን ውጤታማ ተግባራት ይበልጥ ለማስፋት ከዓለም ባንክና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያሉ ትብብሮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ፤ የሰው ሀብት ልማትን ለማሳደግ በጤና፣ ትምህርትና ማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ አካታች ልማትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ለጀመረቻቸው ተግባራት የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የፎረሙ ዓላማ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎችን በማሳተፍ የኢትዮጵያን የሰው ሀብት ልማት ለማሻሻል የሚያስችሉ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ላይ ለመወያየት መሆኑ ተገልጿል።