ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ እያከናወችው ያለው የኃይል አማራጭ የማስፋት ሂደት የሚደነቅ ነው

ሆሳዕና ፤ መስከረም 22/2018 (ኢዜአ) :- ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ እያከናወችው ያለው የኃይል አማራጭ የማስፋት ሂደት የሚደነቅ ነው ሲሉ  የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ውጣ ውረድ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወቃል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት ሲሆን መንግስት በቀጣይም ሌሎች የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በሂደት ላይ ነው።

በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ግዙፍ ኤርፖርት፣ የኒውክሌር ፋብሪካ፣ የጋዝ ፋብሪካ እና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑ ይሆናል።  

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ እያከናወችው ያለው የኃይል አማራጭ የማስፋት ሂደት የሚደነቅ ነው።

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ የኃይል አማራጭ ከማስፋት በዘለለ ሌሎች የኃይል አማራጮችን ወደ ስራ ለማስገባት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው በሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ተመስገን ቶማስ ለኢዜአ እንደገለፁት ግድቡን ለማጠናቀቅ የተደረገው የተቀናጀ ጥረት የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም ለመልማትና ለማደግ ያለውን ቁጭት ያሳየ ነው፡፡


 

መንግስት ያቀዳቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ ሌሎች የኃይል አመራጮችን ለማስፋት እየሄደበት ያለው መንገድ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም እነዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከግብ ለማድረስ ድርሻው የጎላ መሆኑን አንስተው ህዝቡ በጠንካራ ትብብር ይህን ፕሮጀክት እውን በማድረጉ ትልቅ ታሪክ ሊሰራ መቻሉን አመልክተዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አስራት ኤርሞሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ሌሎች የኃይል አማራጮችን በማስፋት ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትን ለማምጣት እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።


 

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅም ኢትዮጵያ የተለመቻቸውን ኃይል የሚፈልጉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ገንብታ ጥቅም ላይ እንድታውል ሚናው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በተለይም ከውጭ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ እንደ ቀዳሚ መስፈርት የሚጠቀሰውን የኃይል አማራጭ በመያዟ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም