ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቋል
ድሬዳዋ ፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡለትን አዳዲስ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ነባር ተማሪዎቹን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት መገርሳ ቃሲም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሪፎርሞችን በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ኃይል እያፈራ ይገኛል።
"የአፕላይድ ሳይንስ' የትኩረት መስኩ የሆነው ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮም በቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በጤናው ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
በዩኒቨርስቲው የኢ-ለርኒግ' ስራን ለማቀላጠፍ ዘመናዊ የዲጂታል ስቱዲዮ ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባቱን እና ዘመናዊ የሪፈራልና የማስተማሪያ ሆስፒታል በከፊል አገልግሎት ማስጀመሩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን አክለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የድሬዳዋን የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የመሆን ራዕይ ለማሳካት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በጥናትና ምርምር ዘርፍም ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ በኢንዱስትሪዎች እየቀሰሙ የሚገኙት የተግባር ዕውቀትና ክህሎት የአገርን የብልጽግና ጉዞ በላቀ ብቃት ለማሳካት እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ የሚገኙ ተማሪዎችን የማስተማር ስራ በዚህ ሳምንት መጀመሩን ጠቅሰው ዩኒቨርስቲውን ምርጫቸው አድርገው የሚመደቡ አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት አጠናቆ እየተጠባበቀ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪም ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን እንዲሁም የማህበረሰቡን ማህበራዊ ችግሮች የማቃለል ተልዕኮውን አጠናክሮ ቀጥሏል ።
በ1999 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራ የጀመረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ሰዓት በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ከ42 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ እያስተማረ ይገኛል።