ቀጥታ፡

በክልሉ የማሰልጠኛ ተቋማትን አቅም በማሳደግ በክህሎት የበቃ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው

ሚዛን አማን፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆችን አቅም በማሳደግ ተወዳዳሪ ትውልድን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

ኮሌጆች በቴክኖሎጂ ታግዘው ዲጂታል አሰራርን  እንዲያጠናክሩ የሚያስችሉ ተግባራት በቀጣይ በትኩረት እንደሚከናወኑም ተመላክቷል።

በቢሮው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ካሳሁን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በክልሉ  የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጆችን አቅም በማሳደግ በክህሎት የበቃ ትውልድ ለመፍጠር እየተሠራ ነው።

የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች  ሥራ ፈጣሪዎችን እንዲያፈሩ ተቋማቱን  የማደራጀት ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

ለዚህም የኮሌጆችን አቅም በግብዓትና በሰው ኃይል በማጠናከር ሰልጣኞችን ወቅቱ የሚጠይቀው እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ መሰራቱን  ተናግረዋል።

አቶ ለገሰ እንዳሉት በተሻሻለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ፖሊሲ መሠረት በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ኮሌጆችን በቴክኖሎጂ በማጠናከር ዲጂታል አሰራርን እንዲተገብሩ  ትኩረት ተሰጥቶታል።

የአማን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን አለማየሁ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ገበያው የሚፈልገውን የበቃ የሰው ሀይ ለማፍራት  የኮሌጆችን አቅም ማሳደግ ይገባል።


 

ኮሌጁ በተሻሻለው የትምህርት አሰጣጥ ስትራቴጂ መሠረት የአካባቢውን የልማት ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የሥልጠና መስኮችን ለመስጠት ግብዓት በማሟላት ዝግጅት ማድረጉን  ተናግረዋል።

የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ኮሚሽን አለማየሁ በበኩላቸው የኮሌጁን አቅም ለማሳደግ ለአሰልጣኞች  የሥራ ላይ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን  ጠቁመዋል።


 

ይህም  የመማር ማተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ተማሪዎች በሥልጠና ብቁና ተወዳዳሪ  ሆነው የሚወጡበትን አቅም ለመፍጠር ማገዙን  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም