ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ የልማት ኢኒሼቲቮችን በስኬታማነት እየተገበረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ የልማት ኢኒሼቲቮችን በስኬታማነት እየተገበረች ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸውን የልማት ኢኒሼቲቮችን በስኬታማነት እየተገበረች እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት ጋር በመተባበር የምግብና የግብርናው ዘርፍና የባዮ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አውደ ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን፤የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የባዮሎጂካልና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት ሁለንተናዊ ልማትን ለማሳለጥ አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አፍሪካ የዜጎቿን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሊለማ የሚችል ሰፊ የእርሻ መሬት ቢኖራትም የምግብ ምርቶችን አሁንም ከውጭ እንደምታስገባ አስረድተዋል።
ከዚህ ለመላቀቅ የባዮሎጂካልና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓትን በማላመድ የአርሶ አደሮችን የግብርና ምርታማነት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተገበረቻቸው የሚገኙ የልማት መርሃ ግብሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው በስኬታማ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ፣በሌማት ትሩፋት፣በስንዴ ምርታማነትና በሌሎች የግብርና መርሃ ግብሮች የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት ሰብሳቢ ባሊሬይን ሀኪም፤የአህጉሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ የግብርና ምርታማነት የአፍሪካውያንን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የሥርዓተ ምግብና የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ደህንነት ጥረቶችን የሚያግዙ መርሃ ግብሮችን በመተግበር ለግብርና ምርታማነት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።