የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ከመዝናኛነታቸው ባለፈ ውብና አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ከመዝናኛነታቸው ባለፈ ውብና አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ከመዝናኛነታቸው ባለፈ ውብና አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ለአየር ብክለት መቀነስ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመዲናዋ የህዝብ መዝናኛ ስፍራ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
በመዲናዋ የተለያዩ ነባርና አዳዲስ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ለአዋቂም ሆነ ለህጻናት በሚመች መልኩ ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ስፍራዎቹ ከመዝናኛነት ባለፈ ውብና አረንጓዴ አካባቢ በመፍጠር ለአየር ብክለት መቀነስ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
በእንጦጦ ፓርክ ሲዝናኑ ያገኘናቸው አሜሪካዊቷ አማንዳ ኮልማን በአዲስ አበባ ከሰባት ዓመት በላይ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በቆይታቸው በመዲናዋ በየጊዜው ሰፋፊና ውብ የሆኑ የመዝናኛ ቦታዎች መገንባታቸውን ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
በተለይም የእንጦጦ ፓርክ በአረንጓዴነቱ፣ በነፋሻማነቱና በውስጡ በያዛቸው መዝናኛዎቹ የተለየ መሆኑን ገልጸው፤ በአካባቢው ያለው ደንና ንጹህ አየር አዝናኝና ማራኪ ነው ብለዋል።
እንደ እንጦጦ ያሉ መዝናኛ ፓርኮች በከተማው መኖራቸው አካላዊና ስነ ልቦናዊ እረፍት ለመውሰድ፣ ድካምና ውጥረትን ለማቃለል፣ የውስጥ እርካታ ለማግኘትና መንፈስን ለማደስ ወሳኝ መሆናቸውን ወይዘሮ ምህረት ይስሀቅ ጠቅሰዋል።
ውብና አረንጓዴ የሆኑ መዝናኛ ስፍራዎች የአየር ብክለትን ለመከላከልና ንጹህ አየር ለመተንፈስ ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል ።
በኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ልጆቻቸውን ሲያዝናኑ ያገኘናቸው አቶ ደረጀ መኩሪያ በፓርኩ የተለያዩ የአዋቂዎችና የህጻናት መዝናኛዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ልጆችን በተሟላ የመዝናኛ ቦታ ማዝናናት አዕምሯቸው ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆንና የተለያዩ ትምህርታዊ ልምዶች እንዲቀስሙ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተማሪ ኤልሻዳይ ታምሩ በበኩሏ እረፍት ስትሆን ወደ ፓርኩ በመምጣት ራሷን እንደምታዝናና ተናግራ ፓርኩ የያዛቸው መጫወቻዎች በውስጣቸው ትምህርት ያዘሉ መሆናቸውን ጠቅሳለች።
በአዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ነፃነት ዳባ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ውብ፣ ሳቢና ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን ደረጃ ማሻሻልና አዳዲስ ግንባታ ማከናወን አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎቹ ለቱሪስት መስህብነትና ገቢ ለማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በርካታ ብርቅዬ እንስሳትና አዕዋፋት በፓርኮቹ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ተጨማሪ መስህቦችን ለማካተት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡