የአዲስ አበባ የልማት ስራዎች የከተማዋን የዲፕሎማቲክ ማዕከልነት በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው-በኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የልማት ስራዎች የከተማዋን የዲፕሎማቲክ ማዕከልነት በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው-በኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ተወዳዳሪነት በማሳደግ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን በተግባር የሚያረጋግጡ መሆኑን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣አፍሪካ ህብረትና በኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር ሮድሪጎ ጉዝማን ገለፁ።
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣አፍሪካ ህብረትና ኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር ሮድሪጎ ጉዝማን ለኢዜአ እንዳሉት፤ቺሊና ኢትዮጵያን በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።
ሁለቱም አገራት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው መሆናቸውን አንስተው፤ ቺሊ በደቡብ ለደቡብ ትብብር ከአፍሪካ አገራት ጋር ትስስር ያላት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አፍሪካ ብዝሃ ሀብት ያላት አህጉር በመሆኗ ብዝሃ ዘርፍ ትብብራችንን ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
አምባሳደሩ ግጥምና ሙዚቃን በመሳሰሉ የኪነ ጥበብ ስራዎች የሁለቱን አገራት የባህል ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
የአገራቱን የባህል ትስስር በማጎልበት የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ነው ያሉት።
ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች የበለጠ እንዲተዋወቁ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ነው ያስረዱት።
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና የዲፕሎማቲክ ማዕከል በመሆኗ በከተማዋ የተደረገው ለውጥ ውበትና ዘመናዊነትን ያላበሳት መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ መዲናዋን ዘመናዊና ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።