በምርት ዘመኑ ከ84 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ኩንታል የቅባትና ጥራጥሬ ሰብል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በምርት ዘመኑ ከ84 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ኩንታል የቅባትና ጥራጥሬ ሰብል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ በተያዘው የ2017/18 የምርት ዘመን ከ84 ሚሊየን 696 ሺህ ኩንታል በላይ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብል ምርት እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በምርት ዘመኑ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች የመኸር እርሻ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን በሚኒስቴሩ የቅባት ሰብሎች ልማትና ድኅረ ምርት ዴስክ ኃላፊ ፍሰሐ ቶሎሳ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ ሐረሪ ክልሎች እና ድሬዳዋ አሥተዳደር 2 ሚሊየን 701ሺህ 989 ሔክታር መሬት በቅባት ሰብሎች ለማልማት መታቀዱን ጠቁመዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም 2 ሚሊየን 633ሺህ 843 ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህም 40 ሚሊየን 104 ሺህ 279 ኩንታል የቅባት ሰብል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ 2 ሚሊየን 293 ሺህ 836 ሔክታር በጥራጥሬ ሰብል ዘር ለመሸፈን መታቀዱን ጠቅሰዋል።
እስካሁን 1 ሚሊየን 991 ሺህ 215 ሔክታር በጥራጥሬ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው፤ እንደ ሽንብራ ያሉ ሰብሎች በቀጣይ የዘር ወቅታቸው ስለሚጠናቀቅ የመሬት ሽፋኑ ይጨምራል ብለዋል።
ከዚህም 44 ሚሊየን 592ሺህ 333 ኩንታል የጥራጥሬ ሰብል እንደሚገኝ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በቅባት ሰብል ከተሸፈነው 2 ሚሊየን 633 ሺህ 843 ሔክታር፤ 2 ሚሊየን 54 ሺህ 866 ሔክታር መሬት ላይ ያለው የሰሊጥና አኩሪ አተር ሰብል መሰብሰብ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የአኩሪ አተር ምርት በስፋት በተዘራባቸው አካባቢዎች በአኩሪ አተር ማጨጃ ማሽን ጭምር ሰብል የመሰብሰብ ሥራው እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ማሽኑ ያላቸው የግል ድርጅቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የቅባት ሰብሎችን በስፋት በማምረት የምግብ ዘይት ፋብሪካዎችና የኤክስፖርት ገበያ ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።