ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚን በመተግበር ለአካባቢ ተስማሚ  ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚን በመተግበር ለአካባቢ ተስማሚ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኗን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ  ገለጹ።

ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ መድረክን አካሂዷል።


 

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በዚሁ ወቅት፤ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ለአካባቢ ምቹ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረቱ የስራ እድሎችን ለማስፋት፣ የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር ወሳኝ መሰረት ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል፣ ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም አቅምን በማጠናከር አካባቢ ላይ ጉዳት የማያስከትል የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ለስኬቱም ብሔራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ይፋ መደረጉን ጠቅሰው፥ ለፍኖተ ካርታው ትግበራ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን በማንሳት፥ የግሉ ዘርፍና  የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ30 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ያሳተፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች መከናወናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ሁለት ወራት ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ጠቁመዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሔለን ደበበ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሰርኩላር ኢኮኖሚ መድረክን እንድታካሂድ መመረጧ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እያስመዘገበች ላለው ውጤታማነት እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል።


 

የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታው ለአካባቢ ብቻ ሳይሆን ለስትራቴጂክ ልማት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

አዳዲስ የእሴት ሰንሰለቶችን ለመፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ጥገኝነትን ለመቀነስ  የከተማና የገጠር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እድሎችን የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

ለፍኖተ ካርታው ትግበራ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅሰው አፍሪካውያን በአንድነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አካታች ኢኮኖሚ መገንባት እንችላለን  ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ፊንላንድ የመጀመሪያውን ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ያደረገች ሀገር መሆኗን ገልጸው በዘርፉ ያላትን የበርካታ አመታት ልምድ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚን ማሳካት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ግንባር ቀደም በመሆን ለሌሎችም አርአያ የመሆን አቅም እንዳላት ተናግረዋል።

በጀርመን የልማት ተራድኦ ደረጅት የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ፕሮግራም ማናጀር ጀምስ ኔጅሩ ብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ውጤታማ እንዲሆን በጋራ መስራት ያስፈልገናል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ረገድ በአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን ለሌሎችም አርአያ እንደምትሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሰርኩላር ኢኮኖሚ ( መልሶ መጠቀም ) ለአካባቢ፣ ለኢኮኖሚ፣ ለኢንዱስትሪ እድገት ፤ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም