ኢትዮጵያ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት ሜርኩሪ ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክለው "የሚናማታ" ዓለም አቀፍ ስምምነት ትግበራ እንዲሳለጥ በቁርጠኝነት ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት ሜርኩሪ ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክለው "የሚናማታ" ዓለም አቀፍ ስምምነት ትግበራ እንዲሳለጥ በቁርጠኝነት ትሰራለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት ሜርኩሪ ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክለው የ"ሚናማታ" ዓለም አቀፍ ስምምነት ትግበራ እንዲሳለጥ ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።
የቆዳ ውበትን ለማስጠበቅ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የሚጨመረው ሜርኩሪ የተሰኘው ኬሚካል ለሰው ጤናና አካባቢ ብክለት መጨመር አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።
የሜርኩሪ ኬሚካል በምርቶቹ ውስጥ እንዳይጨመር ለማድረግ የወጣውን ዓለም አቀፍ የሚናማታ ሥምምነት በርካታ አገራት ፈርመዋል።
ሥምምነቱ በአፍሪካ አገራት እንዲተገበር ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱ የተገለጸ ሲሆን በፕሮጀክቱ ቀጣይ ትግበራ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የልማት አጋሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በኋላ መተግበር የሚጀምር ሲሆን በዓለም አቀፍ አካባቢ ጥበቃ ፋሲሊቲ የፋይናንስ ድጋፍ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም አስተባባሪነት የሚተገበር ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ13 የአፍሪካ አገራት የሚተገበር ሲሆን ሜርኩሪ የተጨመረባቸው የቆዳ ማስዋቢያ ምርቶች ዝውውር፤ ንግድና አቅርቦት ሰንሰለትን መቁረጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሜርኩሪ የተጨመረባቸው ምርቶችን መቀነስ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ማድረግ እና ቁጥጥርን ማጠናከር፣የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ከዓላማዎቹ መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ እንዳሉት፤ ሜርኩሪ በአካባቢ ብቻ ሳይሆን በሰው ጤናና ቀጣይ ትውልድ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነው፡፡
ሴቶችና ታዳጊ ህጻናት የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሜርኩሪ የተጨመረባቸው ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ሜርኩሪ የተጨመረባቸው የቆዳ ማስዋቢያ ምርቶች አሁንም ገበያ ላይ መኖራቸውን ገልጸው፤ ምርቱ እንዳይመረት ማድረግ እና የአቅርቦት ሰንሰለቱን መቁረጥ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሚናማታ ዓለም አቀፍ ስምምነትን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቋን ጠቅሰው ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ማርጋሬት ኡዱክ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሜሪኩሪ የተጨመረባቸው የቆዳ ማስዋቢያ ምርቶች በሰው ጤናና አካባቢ ሥነ ምህዳር ላይ የሚፈጥረው ቀውስ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለማበጀት በትብብር እና ወቅታዊ እርምጃዎችን መውሰድ የሚገባን ወቅት ላይ ነን ያሉት ተወካይዋ ሳይንሳዊ አሰራሮችን በመከተል እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሚናማታ ሥምምነት ዋና ጸሃፊ ሞኒካ ስታንኪዊዝ በበኩላቸው፤ የሚናማታ ሥምምነት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ እጅ ለዕጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ የተጀመረው አውደ ጥናትም ሥምምነቱ በአፍሪካ ደረጃ በተሻለ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ሳራይ ማሉሞ እንዳሉት፤ፕሮጀክቱ በአፍሪካ በሙሉ አቅሙ ተተግብሮ ውጤታማ እንዲሆን የዓለም የጤና ድርጅት የሚጠበቅበትን ድርሻ ይወጣል።
ለዚህም በባለሙያ እንዲሁም በፖሊሲ ጉዳዮችና ዙሪያ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።