በዋግ ኽምራ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን ማረጋገጥ ተችሏል- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
በዋግ ኽምራ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን ማረጋገጥ ተችሏል- ምክር ቤቱ

ሰቆጣ ፤ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን በተደረገ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉን የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንታይቱ ካሴ ገለጹ።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 31ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው የመክፈቻ መድረክ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ፋንታይቱ ካሴ ባደረጉት ንግግር፤ በ2017 የበጀት ዓመት አስተዳደሩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን በክትትል ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
በሕብረተሰቡ ዘንድ የልማት ጥያቄ ሆኖ የቆየው የሰቆጣ-ብልባላ- ጋሸና የአስፋልት ፕሮጀክቶች ምላሽ ያገኘበት በጀት ዓመት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የአካባቢውን እምቅ ፀጋ ለመጠቀም እቅድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ እቅዱ እውን እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
አፈ ጉባኤዋ፤ የታለቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ከዘመናት ቁጭት የወጣንበት ከመሆኑም ባለፈ የሃገራችንን ዘላቂ እድገት መሰረት የጣለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ከፍተኛ መነሳሳት የፈጠረ እንደሆነም አመልክተው፤ የዞኑ ህዝብም ለግድቡ ግንባታ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው፤ ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲቀርብ መደረጉ በመኸር ወቅት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ይሕም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ በአስተዳደሩ ደረጃ ለማሳካት መሰረት የጣለ መሆኑን አመልክተዋል።
በሰቆጣ ከተማ ዛሬ የተጀመረው የምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታ ያለፈው በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድን መርምሮ እንደሚያፀድቅ ተመልክቷል።