ቀጥታ፡

ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራና የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የሕብረተሰብ ጤናን ስጋቶችን በጋራ መከላከል ያስችላሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራና የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የሕብረተሰብ ጤናን ለአደጋ የሚያጋልጡ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ለሰዎች ደህንነት፣ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ሥርዓት ምግብን ለማረጋገጥ፣ የጤና ስጋትን በዘላቂነት ለመቋቋም ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ እና አካታች የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘጋጅታለች።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ ሁለቱ ዕቅዶች የዓለም አቀፍ የጤና ህግጋትና የኢትዮጵያን ልምድ መሰረት አድርገው የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የሕብረተሰብ ጤናን ለአደጋ የሚያጋልጡ ስጋቶችን በመተንበይ፣ ቀድሞ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ስትራቴጂው ከሰው ጤና ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ለህብረተሰብ ጤና መጠበቅም የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል እና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

የአንድ ጤና ስልታዊ ዕቅድና ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ ዕቅድ በአንድ ተቋም ብቻ ውጤታማ አይሆኑም ያሉት ሚኒስትሯ፤ መንግስት፣ የአጋር አካላትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብርን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ መግቢያና መውጫዎች ያሏት ሀገር መሆኗ መልካም አጋጣሚዎች ቢሆኑም ለበሽታ ስርጭት የራሳቸው አሉታዊ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የፈረመችውን የዓለም የጤና ደንብ መሰረት በማድረግ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአየርና በየብስ ድንበር ላይ የበሽታ ቁጥጥርና ቅኝት እንደምታደርግ አንስተው፤ ብሔራዊ ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ስራዎችን ወደ አንድ ዕቅድ፣ አንድ በጀትና አንድ ሪፖርት ማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢፋ ሙለታ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ዕቅዶቹ ከምርት ጀምሮ እስከ ምገባ ድረስ ያለውን ስርዓት ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ አጋዥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የሕብረተሰቡን የጤና አጠባበቅ ስርዓት ከምግብ ደህንነትና ይዘት አንጻር የተሟላ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ የሰዎች፣ እንስሳት፣ አካባቢና ዕፅዋት ጤና ማረጋገጥ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረ መሆኑን ገልጸው፣ ለስልታዊ ዕቅዱ ትግበራ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ዛሬ ይፋ የተደረጉት ዕቅዶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ የጤና ስርዓት የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

በዓለም አቀፍና በብሔራዊ ደረጃ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን ቀድሞ መከላከልና ምላሽ ለመስጠት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ በማንሳት፥ ኢንስቲትዩቱ ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ፤ ኢትዮጵያ የዜጎችን ጤና አጠባበቅ ስርዓት ለማዘመን የምታደርገው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያን መንግስት የአመራር ሰጭነት ብቃት አድንቀዋል።

የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፤ ፋኦ የኢትዮጵያን የእንስሳት ጤና እና የአካባቢ ጥብቃ ስርዓት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የጤና ስርዓት ለመገንባት የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።

የአምስት ዓመት የአንድ ጤና ስልታዊ ዕቅዱ እ. አ.አ ከ2025/26 እስከ 2029/30 የሚተገበር ሲሆን፥ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ ዕቅድ ደግሞ እ.አ.አ እስከ 2028/29 ይተገበራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም