ቀጥታ፡

የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- የፀጥታ ተቋማት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፦ የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን የፀጥታ ተቋማት አስታወቁ።

የፀጥታና ደህንነት አካላት አመራሮች በፀጥታ ተቋማት ዝግጅት ዙሪያ ተወያይተዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ መስከረም 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአንድነት እና የአብሮነት በዓል የሆነው የኢሬቻ በዓል በስኬት እንዲከበር የፀጥታና ደህንት ተቋማት ከበዓሉ አከባበር ኮሚቴዎች፣ ከኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት፣ ከሀደ ስንቄዎች፣ ከፎሌዎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በዓሉን ለማክበር የሚመጡ በመሆኑ አስፈላጊው የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በሠላም እንዲጠናቀቅ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የሰላም ሰራዊት አባላት በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ሸገር ከተማ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡


 

ሕብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት ሆነ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት በፌዴራል ፖሊስ የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (citizen engagement application) ጨምሮ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም