ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ታስተናግዳለች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ የከተማ ተራራ ላይ የብስክሌት ውድድር (City Mountain Bike Race) በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ውድድሩ ከመጋቢት 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል። 

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 98ኛው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ የነበራትን ተሳትፎ እና ቀጣይ ስራዎች አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።


 

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ብስክሌት ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድሙ ኃይሌ ዓለም አቀፍ የከተማ ተራራ ላይ ብስክሌት ውድድሩ በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

በውድድሩ ላይ ከ25 ሀገራት የተወጣጡ ከ110 በላይ ብስክሌተኞች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን የሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ከተሳታፊዎቹ መካከል እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

ውድድሩ ዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (UCI) የውድድር መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተ እና እውቅና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስችል ዝግጅት መጀመሯንና መንግስት ለዝግጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ ውድድሩ በኢትዮጵያ መደረጉ ሀገሪቷ በአፍሪካ ደረጃ በብስክሌት ስፖርት እያስመዘገበች ያለው አመርቂ ውጤት ማሳያ እንደሆነም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም