በመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ ለተገነባው "የድሬዳዋ እመርታ" ቤተ መጻሕፍት የግብዓት ማሰባሰብ ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ ለተገነባው "የድሬዳዋ እመርታ" ቤተ መጻሕፍት የግብዓት ማሰባሰብ ስራ ተጀመረ
ድሬደዋ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ በመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ የተገነባውን "የድሬዳዋ እመርታ" ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያግዝ የግብዓት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በድጋፍ ማሰባሰቡ መርሃ ግብር ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ የአስተዳደሩ ተቋማት፣ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት እና ሌሎች የፌደራልና የአስተዳደሩ ተቋማት የመፅሐፍት ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉን የተረከቡትና መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ናቸው።
አቶ ገበየሁ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የእርስ በእርስ የመደጋገፍና መተባበር ኢትዮጵያዊ እሴቶች የትኛውንም ማህበራዊ ችግሮች በራስ አቅም ለመፍታትና ለመሻገር ያስችላሉ ብለዋል።
ዛሬ በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ እና በአስተዳደሩ በጀት በ475 ሚሊዮን ብር ለተገነባው የእመርታ ዘመናዊ ቤተመጻሕፍት የተደረገው ድጋፍ እና የተገባው ቃል የዚሁ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በመሆኑም አንባቢ፣ ተመራማሪና አገር ገንቢ ትውልድ የማፍራቱን ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ያለውን የእርስ በእርስ መደጋገፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ታሪኩ በበኩላቸው በድሬዳዋ የተገነባው የእመርታ ዘመናዊ ቤተመጻሕፍት አንባቢና ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው አንስተዋል።
ዛሬ ከለገሱት 10 ሺህ የተለያዩ መጻሕፍት በተጨማሪ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠትና ሌሎች ድጋፎች በማድረግ ቤተ-መፅሐፉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደግፋለን ብለዋል።
የተገነባው የእመርታ ቤተመጻሕፍት ደረጃውን የጠበቀና ለማንበብ የተመቸ መሆኑን የገለፁት ደግሞ 500 የተለያዩ መጻሕፍትን የለገሱት የኢትዮጵያ ቤተመጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ተወካይ አቶ እስራኤል በዙ ናቸው።
ቤተመጻሕፍቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ በሁሉም መስክ የመደጋገፍና የመተባበር ጉዞን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
መፅሐፍት የለገሱት የድሬዳዋ ወረዳ ሁለት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ በበኩላቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የታየውን የመደጋገፍ ባህልን አጠናክሮ በማስቀጠል ቤተመጻሕፍቱ አገልግሎት እንዲጀምር እንረባረባለን ብለዋል።
"የድሬዳዋ እመርታ" ቤተመጻሕፍት ከመደመር መፅሃፍ ሽያጭ እና በአስተዳደሩ በጋራ 475 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን ጥላሁን ለኢዜአ ገልጸዋል።