ለኢሬቻ በዓል የትራንስፖርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል -የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለኢሬቻ በዓል የትራንስፖርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል -የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ለኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይኖር በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል የትራንስፖርት አገልግሎትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አሰፋ ሃዲስ እንዳሉት በመጪው መስከረም 24 እና 25 በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተማ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
በዓሉን ተከትሎ የትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር እንዳይፈጠር ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከፐብሊክ ሰርቪስ እንዲሁም ከኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ጋር በመቀናጀት ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።
በተለይም ለሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ አከባበር ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ ለሚያቀኑ የበዓሉ ታዳሚዎች በመዲናዋ በሚገኙ ስድስት መናኸሪያዎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።
እንዲሁም ከለቡ መስመር እስከ ቢሾፍቱ የበዓሉን ታዳሚዎች የሚያደርስ ባቡር መዘጋጀቱን አንስተው ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርትም ወደ ባቡሩ ለማድረስ ከ50 በላይ ተሽከርካሪዎችን መመደቡን ተናግረዋል።
በዚህም በአዲስ ከተማ ትልቁና ትንሹ መናኸሪያ፣ አስኮ፣ አየር ጤና፣ ቃሊቲና ላምበረት በሚገኙ መናኸሪያዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ከመናኸሪያዎች በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ የተለያዩ የመነሻ ቦታዎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተዘጋጀም እንዲሁ።