የኢሬቻ በዓል አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እሴቱን ጠብቆ ይከበራል -የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እሴቱን ጠብቆ ይከበራል -የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት
ቢሾፍቱ ፤መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፡- የኢሬቻ በዓል አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እሴቱን ጠብቆ እንደሚከበር የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አስታወቀ።
የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አባላት የዘንድሮውን የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል የተመለከተ የጋራ መግለጫ በሆረ አርሰዲ ሰጥተዋል።
የህብረቱ አባል አባገዳዎች በሰጡት መግለጫ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪውን ጊዜ በተስፋ የሚቀበልበት ነው ብለዋል።
በዓሉ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ሰላምና ፍቅር የሚገለጽበት እንዲሁም አብሮነትና አንድነት የሚጠናከርበት ትልቅ አገራዊ እሴት መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ ደግሞ የዘንድሮውን ኢሬቻ በዓል ልዩ የሚያደርገው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጠናቀቀበት ማግስት በመሆኑ ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል በተሻለ መልኩ እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
በዓሉ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት ትልቅ የአደባባይ በዓል መሆኑን ጠቁመው በዓሉን በተለመደው መልኩ በጎ እሴቱን በሚገባ በማንጸባረቅ መከበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎችም ኢሬቻ ባህል እና እሴቱ በሚፈቅደው መሰረት እርጥብ ሳር እና አበባ ይዘው፣ በባህል አልባሳት ተውበው በዓሉን እንዲያደምቁ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሆነና ለአገር ማንሰራራትም ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና የውጪ አገር ዜጎች ጭምር እንዲታደሙበት ግብዣ አቅርበዋል።