በጋምቤላ ክልል የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ አመራሩ መትጋት አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ አመራሩ መትጋት አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ክልልን እድገት በማፋጠን የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ አመራሩ በትጋት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በብልጽግና ፓርቲ ከጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ አመራር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ለአካባቢው ልማት መፋጠን ይበልጥ መስራት አለበት ብለዋል።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
አመራሩ የክልሉን የመልማት ጸጋዎች በመጠቀም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በጊዜ የለኝም መንፈስ መትጋት እንዳለት አስገንዝበዋል።
ለዚህም ከአቅም ግንባታ ስልጠናው የተገኘውን የአመራርነት ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝብ አገልጋይነቱን ማሳደግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ አመራሩ ያለውን እውቀትና ልምድ አስተባብሮ መስራት ከቻለ ክልሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይበልጥ መለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል።
በተለይም ክልሉ ያለውን ሰፊ የመልማት አቅም ካለው የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ ከተሰራ ባጠረ ጊዜ የክልሉን ልማት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
በክልሉ ለተጀመረው የልማት ስራዎች ስኬታማነት የድጋፍና የትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በጋምቤላ ከተማ ሲሰጥ በቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።