ኢትዮጵያ በዓለም ብስክሌት ሻምፒዮናው አፍሪካን ያኮራ ውጤት አስመዝግባለች - የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም ብስክሌት ሻምፒዮናው አፍሪካን ያኮራ ውጤት አስመዝግባለች - የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና አፍሪካን ያኮራ ውጤት ማስመዝገቧን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 98ኛው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ የነበራትን ተሳትፎና ቀጣይ ስራዎች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ከመስከረም 11 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ሻምፒዮና ከ108 ሀገራት የተውጣጡ 769 ብስክሌተኞች በ13 የውድድር አይነቶች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በአምስት የውድድር አይነቶች ተሳትፋ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ አጠናቃለች።
የግል ሰዓት ሙከራ፣ የጎዳና ላይ ውድድርና ድብልቅ ሪሌይ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍጹም ወልደአብ 15 አባላት የያዘ ልዑክ ቡድን በብስክሌት ሻምፒዮና ላይ መሳተፉን ገልጸዋል።
ለዓለም የብስክሌት ሻምፒዮና አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም አመልክተዋል።
በኬንያ የተካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናና በቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ለዓለም ሻምፒዮናው እንደ መዘጋጃ ያገለገሉ ውድድሮች ናቸው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የብስክሌት ማህበር(ዩሲአይ) ባዘጋጃቸው የስልጠና እድሎች ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች በኬንያ፣ ፈረንሳይ እና ደቡብ አፍሪካ የስልጠና እድሎች ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
በመቀሌ በተካሄደው የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ብስክሌተኞች በሻምፒዮናው ላይ መሳተፋቸውን ነው ኃላፊው የገለጹት።
ፅጌ ካህሳይ እ.አ.አ በ2028 በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው 34ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የብስክሌት ውድድር ዝግጅት የስልጠና እድል ማግኘቷ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
አጠቃላይ የነበረው ዝግጅት ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት እንድታገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ብስክሌት ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወንድሙ ኃይሌ ኢትዮጵያ በኪጋሊ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አፍሪካን ያኮራ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
በዓለም ብስክሌት ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ሚኒማ ያሟሉ በርካታ ብስክሌተኞች ማሳተፏን አመልክተዋል።
108 ሀገራት በተሳተፉበት ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአምስት የውድድር አይነቶች በመሳተፍ በጎዳና ላይ ውድድር ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ 1ኛ፤ በግል የሰዓት ሙከራ ውድድር ከዓለም 24ኛ ከአፍሪካ 1ኛ፤ በድብልቅ ሪሌይ ውድድር ከዓለም 10ኛ ከአፍሪካ 1ኛ በመሆን በአጠቃላይ ውጤት ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።
በሩዋንዳ ኪጋሊ የተካሄደው 98ኛው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና በአፍሪካ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።