ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር የኢትዮጵያውያን አኩሪ የልማት ቅርስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር የኢትዮጵያውያን አኩሪ የልማት ቅርስ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዓድዋ ድልን የደገመ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር አኩሪ የልማት ቅርስ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም የአፍሪካና ካረቢያን ሀገራት መሪዎች እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት መመረቁ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪክ የሰሩበትና አስተሳሳሪ ትርክት የፈጠሩበት አኩሪ የልማት ቅርስ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዓመታት ተንከባክበውና ጠብቀው ያቆዩዋቸው የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርስና እሴት ባለቤት የሆኑ ህዝቦች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ቅድመ አያቶች ነጭ ወራሪን ድል በመንሳት የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆኑበትን የዓድዋ ድል ያስመዘገቡት የታሪክ ገድልም የአልበገር ባይነት ወኔን ያጎናጸፈ ትዕምርት መሆኑን ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቅድመ አያቶች በደማቸው የፈጸሙትን ገድል በትውልድ ቅብብሎሽ በማሳካት አኩሪ የልማት ድል መፈጸሙን አንስተዋል።
የሕዳሴ ግድብ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የኢትዮጵያውያን መተባበርና አንድነት ጎልቶ የታየበት መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሰው ልጆች ወካይ የዓለም ቅርሶች ባለቤት መሆኗንም ገልጸዋል።
እነዚህ አስደናቂ ሀብቶች ኢትዮጵያን በቅርሶች ክምችት ቀዳሚ ሀገር እንደሚያደርጋት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የቅርስ ጥበቃ ስራ ዜጎችን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማጋመድ ለሀገር አንድነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።
ዜጎች ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፋቸው የዓለም ቅርስ እንዲሆኑ ጭምር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የቅርሶችን ደህንነት የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ስራዎች በማከናወን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።