የጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድና የጤና ደህንነት መርሃ ግብርን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድና የጤና ደህንነት መርሃ ግብርን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦የጤና ሚኒስቴር የአምስት ዓመት ብሔራዊ የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድና የጤና ደህንነት መርሃ ግብርን ይፋ አደርጓል።
የአምስት ዓመት የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2025/26 እስከ 2029/30 የሚተገበር ነው።
ኢትዮጵያ ለሰዎች ደህንነት፣ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ሥርዓት ምግብን ለማረጋገጥ፣ የጤና ስጋትን በዘላቂነት ለመቋቋም አካታች የአምስት ዓመት ብሔራዊ የአንድ ጤና ስትራቴጂያዊ ዕቅድን ቅድሚያ ሰጥታ አዘጋጅታለች።
ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ኢትዮጵያ ሳይንስን መሰረት ያደረገ የጤና አጠባበቅ ስርዓትን ለማንበር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል እ.አ.አ እስከ 2028/29 የሚተገበረው ብሔራዊ የጤና ደህንነት መርሃ ግብር ቀጣይነት ያለው የጤና አጠባበቅ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ ሁለቱ ስትራቴጂ ዕቅዶች የዓለም አቀፍ የጤና ህግጋትና የኢትዮጵያን ልምድ መሰረት አድርገው የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የአንድ ጤና ዕቅድና የብሔራዊ የጤና ደህንነት መርሃ ግብር በአንድ ተቋም ብቻ ውጤታማ አይሆኑም ያሉት ሚኒስትሯ፤ መንግስት፣ የአጋር አካላትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብርን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ዛሬ ይፋ የተደረጉት ዕቅዶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ የጤና ስርዓት የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የዓለም አቀፍ የጤና ህግጋትን ገቢራዊ ማድረግ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፕሮግራሞቹ ገቢራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢፋ ሙለታ በበኩላቸው፣ የሰዎች፣ እንስሳት፣ አካባቢና ዕፅዋት ጤና ማረጋገጥ የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረ መሆኑን ገልጸው፣ ለስትራቴጂና ዕቅዱ ትግበራ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ፣ ኢትዮጵያ የዜጎችን ጤና አጠባበቅ ስርዓት ለማዘመን የምታደርገው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያን መንግስት የአመራር ሰጭነት ብቃት አድንቀዋል።
የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፥ ፋኦ የኢትዮጵያን የእንስሳት ጤና እና የአካባቢ ጥበቃ ስርዓት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የጤና ስርዓት ለመገንባት የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።