በምዕራብ ጉጂ ዞን የሰፈነው ሰላም በአካባቢው የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጉጂ ዞን የሰፈነው ሰላም በአካባቢው የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስችሏል

ቡሌ ሆራ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የሰፈነው ሰላም በአካባቢው የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻሉን አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በዞኑ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መምጣታቸውን ተከትሎ በሰፈነው ሰላም የግብርና ስራን ጨምሮ በሁሉም የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እየተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።
በዞኑ ያለውን ሰላምና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር አባ ገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል።
አባ ገዳዎቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ምልክት የሆነውን የኦሮሞ ገዳ ስርዓት መሰረት በማድረግ ቂምና ቁርሾን በመሻር፣ ጥላቻን በመተው ሰላም መገንባት የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዞኑ ነፍጥ አንስተው በጫካ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች እሴቱን አክብረውና የመንግስትንም የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመምጣታቸው አመስግነዋል።
በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸው በዞኑ ሰላምና መረጋጋት መፍጠሩንና የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ግጭት አሸናፊ የለውም ያሉት አባገዳ ገናሌ አጋ እና የሃገር ሽማግሌ የሆኑት ኦዳ ጎበና፤ የመንግስትን የሰላም ጥሪና የሁላችንንም የሰላም መሻት በመቀበል የመጡ ታጣቂዎችን እናመሰግናለን ብለዋል።
ሌሎችም በጫካ የቀሩ ካሉ ይህን መልካም እድል በመጠቀም ትጥቃቸውን በመፍታትና ወደ ልማት በመመለስ ህዝባቸውን ለመካስ እንዲዘጋጁም መልእክት አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ጉጂ ዞን ጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አየለ ዴባ፤ በዞኑ በርካታ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ እና የአባገዳዎችን የሰላም ጥረት በመቀበል ትጥቃቸውን መፍታታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በዞኑ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ በሁሉም መስኮች የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አረጋግጠዋል።
በዞኑ በሁሉም የቀበሌ መዋቅሮች የተሟላ የመንግስት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንና አርሶ አደሮችም በተሟላ አቅም የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በቀጣይም የመንግስት የሰላም በር ክፍት መሆኑን አንስተው ግጭትና ጦርነትን በመተው የሀገርን ልማትና ማንሰራራት እውን ለማድረግ በትብብር እንስራ ብለዋል።