ማዕከሉ ሰብልን በስብጥር የመዝራት የእርሻ ስነ-ዘዴን በማስተዋወቅ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ ሰብልን በስብጥር የመዝራት የእርሻ ስነ-ዘዴን በማስተዋወቅ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው

ሰቆጣ፤ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፡- የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማእከል ሰብልን በስብጥር የመዝራት የእርሻ ስነ-ዘዴን በማስተዋወቅ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን ገለፀ።
በሰቆጣ ግብርና ምርምር ማእከል የማህበረሰብ ምጣኔ ሃብትና የግብርና ስርፀት ተመራማሪ አቶ አደመ ምህረቱ ለኢዜአ እንደገለፁት ማዕከሉ ሰብልን በስብጥር የመዝራት የእርሻ ስነ-ዘዴን በማስተዋወቅ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው።
በዚህም ሁለት ሰብሎችን በአንድ መሬት ላይ አሰባጥሮ በመዝራት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን ተመራማሪው ገልፀዋል።
በተለይም በመስመር በተዘራ ማሾና ቦሎቄ ሰብል ላይ እንቁ ዳጉሳን አሰባጥሮ በመዝራት ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል።
በዚህም በአበርገሌና ዝቋላ ወረዳ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ላይ 456 አርሶ አደሮች ሰብልን በስብጥር የመዝራት አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል አንድ አይነት ሰብል በሄክታር በመዝራት ይገኝ የነበረውን ዘጠኝ ኩንታል አማካይ ምርት አሁን ላይ ሁለቱን ሰብሎች አሰባጥሮ በመዝራት ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ በአንዱ ሰብል ላይ ጉዳት ሲከሰት በሌላኛው ሰብል በቂ ምርት በማስገኘት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረገ አሰራር መሆኑን አስረድተዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው በያዝነው ክረምት በ70 ሄክታር መሬት ላይ በስብጥር አሰራር በኩታ ገጠም ሰብል ማልማት ተችሏል ብለዋል።
በምርምር ማእከሉ በኩል እየተሰራ ያለው የስብጥር ሰብል ልማት የአርሶ አደሩን የስርዓተ ምግብ ክፍተትን በመሙላት ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዝቋላ ወረዳ የ02 ቀበሌ አርሶ አደር አብጨ መሰለ፤ በሰቆጣ ግብርና ምርምር የቀረበላቸው እንቁ የተሰኘውን የዳጉሳ ሰብል ከማሾ ጋር አሰባጥረው በመዝራት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በወረዳው የ01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጅንን ገብሬ በበኩላቸው አንድ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን እንቁ ዳጉሳን ከማሾ ጋር በማሰባጠር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሰብልን በስብጥር በመዝራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረው፤ ዘንድሮ አሰራሩን በስፋት ለመተግበር እንዲነሳሱ ማድረጉን አብራርተዋል።