ቀጥታ፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት የጥጥ ምርታማነትና ጥራት ማሻሻል በመቻሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘት ተችሏል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሶስት ዓመታት የጥጥ ምርታማነትንና ጥራትን የሚያሻሻሉ ስራዎች በመከናወናቸው የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት አመቺ የሆነ ወደ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ለም መሬት እንዳላት የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።


 

መንግስት ለጥጥ ምርት ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን አቅም በመጠቀም እየጨመረ የመጣውን የጥጥ ፍላጎት ለማሟላትና የዘርፉን አቅም ለመጠቀም እየሠራ ይገኛል፡፡

ለዚህም በጥጥ እሴት ሰንሰለት ላይ ያተኮረ ብሄራዊ የጥጥ ልማት የባለድርሻ አካላት ጥምረት እየተቋቋመ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጥጥ ምርትና ጥራትን በማሻሻል የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን መጠን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተናግረዋል።

በዘርፉ ከተሰማሩት ባለሃብቶች መካከል መልካሙ አብርሃም መንግስት የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ማድረጉ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የጥጥ ምርት የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣ በማስቻል ለውጥ አስገኝቷል ብለዋል።


 

የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች ተደራሽነትን በማስፋፋት አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጥጥ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ጸጋዬ አበበ በበኩላቸው፤ የጥጥ ምርታማነትና ጥራትን በማሻሻል ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በበቂ መጠን ለማቅረብና ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር ዋና ጸሐፊ አጋዚ ገብረየሱስ የጥጥ ምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከዘር አቅርቦት እስከ መጨረሻው ሂደት ደረጃውን ጠብቆ መከናወን አለበት ብለዋል።

የጥጥ ምርት ደረጃውን ጠብቆ አለመመረቱ የጥራት መጓደልና የምርት ብክነት ከማስከተሉ ባለፈ የማምረቻ ወጪ እንደሚጨምር ነው የገለጹት።

በጥጥ ምርት ላይ የሚታየው የጥራት መጓደል የጨርቃጨርቅ ዘርፉን በቀጥታ ተጎጂ ያደርገዋል ብለዋል፡፡


 

በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሳምሶን አሰፋ በዘርፉ ያሉ ችግሮች ተለይተው እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ የጥጥ ምርት እሴት ሰንሰለት ላይ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ብሄራዊ የጥጥ ልማት ጥምረት እየተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።

እሴት የጨመሩ ምርቶችን ማቅረብ፣ የተሻሻሉ አዳዲስ ዝርያዎችን ማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስርና የፋይናንስ ድጋፍን ማጠናከር፣ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎችን ተደራሽነት ማስፋትና ማዘመን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መሪ ስራ አስፈጻሚው ምርታማነትንና ጥራትን የሚያሻሻሉ ስራዎች በመከናወናቸው ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት የምርት መጠን ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን አንስተዋል።

ምርታማነቱ መሻሻል በማሳየቱ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመሸፈን በአነስተኛ መጠን ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 113ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 71ሺህ ሜትሪክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ በቅርቡ በአፋርና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ምርት መሰብሰብ እንደሚጀምር ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የጥጥ ምርታማነትንና ጥራትን የሚያሻሻሉ ስራዎች በመከናወናቸው የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ገቢን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም