የኢሬቻ በዓል የባህላዊ አልባሳት ገበያ የበለጠ እንዲነቃቃ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል የባህላዊ አልባሳት ገበያ የበለጠ እንዲነቃቃ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢሬቻ በዓል የባህላዊ አልባሳት ገበያ የበለጠ እንዲነቃቃ በማድረግ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስገኘላቸው መሆኑን በባህል ልብስ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ገለጹ።
የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ይከበራል።
ኢሬቻ የገዳ ስርዓት አንዱ መገለጫ ሲሆን የአንድነት፣ የወንድማማችነት እና የአብሮነት በዓል ነው።
በኢሬቻ እና በሌሎች በዓላት አከባበር ላይ የሀገር ባህል ልብሶችን የመልበስ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በባህል ልብስ ምርት እና ንግድ ላይ የተሰማሩት እና ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነጋዴዎች፤ ለኢሬቻ በዓል የበርካታ አካባቢ መገለጫ የሆኑ የባህል አልባሳትን በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በባህላዊ አልባሳት ንግድ ላይ ከተሰማሩት መካከል አቶ ሰይፉ ፈይሳ እንዳሉት፤ ኢሬቻ የሥራቸውን ውጤት ይበልጥ ለገበያ የሚያቀርቡበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት በዓል ነው።
በኢሬቻ በዓል ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚሳተፉ በመሆኑ ገቢያቸውም በዛው ልክ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ወጣት ሁንዴ ቶለሳ በበኩሉ ኢሬቻ ትልቅ የኢኮኖሚ ትሩፋት እንዳስገኘለት ጠቁሞ በአዳዲስ ዲዛይን ያሸበረቁ የባህል አልባሳትን ለገበያ ማቅረቡን ገልጿል።
አልባሳት፣ ጌጣጌጦችና ለበዓሉ መዋቢያ የሚሆኑ ቁሶችን የሚሸጡት ወይዘሮ አለም ወርቁ በበኩላቸው ኢሬቻ ስራቸውን ለማስተዋወቅና ገቢያቸውን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
አቶ ገረመው ሌሊሳ በበኩላቸው ኢሬቻ የሀገር ባህል አልባሳትን በስፋት ከማስተዋወቅ ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አለማየሁ ታሪኩ በበኩሉ ለበዓሉ የሚሆን የባህል አልባሳትን አዘጋጅቶ ማቅረቡን ገልጾ ኢሬቻ ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድል እንደፈጠረለትም ተናግሯል።
ወይዘሮ ብዙየሁ ደጀኔ እንደገለጹት በኢሬቻ በዓል የባህል ልብሶችን የመጠቀም ልምድ እያደገ በመምጣቱ ለስራ እድል ፈጠራ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።