ሪያል ማድሪድ በኪሊያን ምባፔ ሀትሪክ ታግዞ ካይራት አልማቲን አሸንፏል - ኢዜአ አማርኛ
ሪያል ማድሪድ በኪሊያን ምባፔ ሀትሪክ ታግዞ ካይራት አልማቲን አሸንፏል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ የካዛኪስታኑን ካይራት አልማቲን 5 ለ 0 ረቷል።
ማምሻውን በኦርታሊክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፈረንሳዊው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በጨዋታ ሁለት እና በፍጹም ቅጣት ምት አንድ አጠቃላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ኤድዋርዶ ካማቪንጋ እና ብራሂም ዲያዝ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ምባፔ በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ አምስት ከፍ አድርጓል። በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን አጠቃላይ ግቦች 60 አድርሷል።
ፈረንሳዊው አጥቂ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 15 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
በጨዋታው ሪያል ማድሪድ በተጋጣሚው ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሎስ ብላንኮሶቹ በስድስት ነጥብ የሻምፒዮንስ ሊጉን የሊግ ፎርማት በስድስት ነጥብ መምራት ጀምረዋል።
በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ካይራት አልማቲ የመጨረሻውን 36ኛ ደረጃ ይዟል።
በተያያዘም ማምሻውን በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ አትላንታ ክለብ ብሩዥን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማርኮ ፓሳሊች በጨዋታ እና ላዛር ሳማርድዚች በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ክሪስቶስ ዞሊስ ለብሩዥ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የሻምፒዮንስ ሊጉ መርሃ ግብር ማምሻውን ቀጥሎ ሲውል ቼልሲ ከቤኔፊካ፣ ጋላታሳራይ ከሊቨርፑል፣ ፓፎስ ከባየር ሙኒክ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ከኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ ኢንተር ሚላን ከስላቪያ ፕራግ፣ ማርሴይ ከአያክስ እና ቦዶ ግሊምት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።