ክልሎች የቱሪዝም ሀብታቸውን በራሳቸው አቅም ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ዕድል ተፈጥሯል - ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎች የቱሪዝም ሀብታቸውን በራሳቸው አቅም ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ዕድል ተፈጥሯል - ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ ክልሎች የቱሪዝም ሀብታቸውን በራሳቸው አቅም ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ዕድል መፈጠሩን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ(ዶ/ር) ገለጹ።
"5ኛው ዙር የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሳምንት" ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በክልላዊው የቱሪዝም ሳምንት ማስጀመሪያ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ(ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
መርሃ ግብሩ የባህልና የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ የዘርፉ ተዋንያን ዘንድ ጠንካራ ትብብርና ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢንቨስትመንትን መሳብና በቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂ ልማት እንዲኖር ማስተዋወቅ፣ የባህል ዲፕሎማሲ ማሳደግ ያስችላልም ተብሏል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ወቅቱ የዓለም የቱሪዝም ሳምንት የሚከበርበት በመሆኑ ካለፈው ሳንምት ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተከበረ ይገኛል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሳምንትም የዚሁ አካል መሆኑን በመግለጽ፤ ክልሎች በራሳቸው አቅም የቱሪዝም ሀብታቸውን በሀገር እና በዓለም ደረጃ የሚያስተዋውቁበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ሳምንቱ ዘርፉን ማሳደግና ኢንቨስትመንትን መሳብ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ መንግስት ለቱሪዝም በሰጠው ትኩረት ለዘርፉ መሰረት የሚጥሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመስጠቱ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉልህ መነቃቃት መፈጠሩን አስታውሰው፤ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለቱሪዝም ለማዋል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ኢኮኖሚውን በመደገፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የፖሊሲ ርምጃዎችን በመውሰድና አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዲጂታላይዜሽን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና በቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ "ቪዚት ኦሮሚያ" የድረገጽ መተግበሪያ እና "ኦሮሚያ ትራቭል ጋይድ" መጽሐፍ ሥራ የጀመረ ሲሆን የክልሉ የቱሪዝም አምባሳደሮችም ተመርጠዋል፡፡
በአምባሳደርነት ከተመረጡት መካከል ገመዳ ኦላና እና ዶክተር ምንተስኖት ፈረደ የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ ገቢ ማስገኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ እነዚህን በአግባቡ በማስተዋወቅ ለዘርፉ እድገት ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡