ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ጋምቤላ፤መስከረም 20/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ በማድረግ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ገለጹ።

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞችንና የአካባቢ ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሃ ግብር ዛሬ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተካሂዷል።


 

በክልሉ በመገኘት መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

የአገልግሎቱ መጀመር ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ዲጂታል መታወቂያውን ዜጎች በብዙ መልኩ እየተገለገሉበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ አገራት ስደተኞች መኖራቸውን አንስተው፤ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ በማድረግ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን መታወቂያ የመስጠት ስራ ጀምረናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠው የዲጂታል መታወቂያ የስደተኞችን ማንነት በሚገልጽ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው በዛሬው እለት በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋምቤላን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ስደተኞችንና የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከርም ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ ሄኖክ ጥላሁን፤ መንግስት በያዘው የእድገትና የለውጥ ምዕራፍ አንዱና አስቻይ ተግባር የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም መሰረት እስካሁን ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እና ስደተኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የሀገሪቱን ዜጎች፣ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ የውጪ ዜጎችና ስደተኞችን በመመዝገብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።


 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው፤ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ዘመኑ ለሚጠይቀው የተሳለጠ አገልግሎት አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸው በክልሉ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም