ቀጥታ፡

የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎትን በማበልጸግ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቷል

ባሕርዳር፤ መስከረም 20/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎትን በማበልጸግ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግና ለማጠናከር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዜጎች በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልጸግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያን ኮደርስ ስልጠና በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡

በዚህም በርካታ ወጣቶች አቅማቸውን ለማሳደግ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማሳደግ ስልጠናውን በኦን ላይ እየወሰዱ ይገኛሉ። 

የአማራ ክልልም ስልጠናውን አጠናክሮ በማስቀጠል ሂደት ላይ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የቻለ ይግዛው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ወጣቱን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት በማበልጸግ የተጀመረውን የዲጅታል ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በበጀት አመቱ ስልጠናውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ካለፈው በጀት ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ 268ሺህ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ አስታውቀዋል።

ስልጠናውን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 197 ወጣቶች ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን አስታውሰዋል። 

ይህም ክንውን ከእቅድ በላይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዕቅድ በላይ ማሳካት የተቻለው በዝግጅት ምዕራፍ ኮሚቴዎችን በማቋቋምና የማሰልጠኛ ተቋማትን በማደራጀት ወደ ስራ በመግባት እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማትና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የማመቻቸት ተግባር መከናወኑን አንስተዋል።

ስልጠናው ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ቴክኖሎጅ ተወዳዳሪ በማድረግ ዘላቂ እድገት ለማሳለጥ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

ወጣቶችም ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት በመቅሰም በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ስልጠና  እንዲወስዱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም